ዓርብ 7 ኖቬምበር 2014

‹‹ወንድሞች ሆይ መጠራታችሁን ተመልከቱ ››


መልዕክት ለወጣቶችና ለወላጆች !
በስመ አብ ወወለድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
ሰንበት በትምህርት ቤቶች በየአጥቢያው ሲመሠረቱ ሊታደጓቸው ከወጠኑት የምዕመናን ክፍል ዋነኞቹ ህጻናትና ወጣቶች መሆናቸው ይታወቃል ፤ብዙ ወጣቶችና ህጻናት በመልካም ስነ-ምግባር መታነጽ የቻሉ ሲሆን አሁንም በዚሁ ሂደት ብዙ ወጣቶቸ በመታነጽ ላይ ናቸው፡፡
ሆኖም ግን በተለያዩ ወቅቶች የተነሱ መናፍቃንና አላውያን ምዕመናንን በተለይ ወጣቶችን እግዚአብሔርን ከሚያመልኩበት ከዕውነተኛው ዕምነታቸው ከተዋህዶ ለመንጠቅ የተለያዩ ባህሪያትን እየተላበሱና ባህሪያቸውን እየቀያየሩ እስከ ቤ/ክ ቅጽር ድረስ ዘልቀው በመግባት በተለይ በወጣቶች ሰ/ት/ቤት ጨዋ መስለውና የበግ ለምድ ለብሰው የኑፋቄ ትምህርታቸውን እጅግ በረቀቀ መንገድ እያራመዱ ጥቂት የማይባሉ ወጣቶችን ማስኮብለል ቢችሉም ኋላ ግን በተለያዩ ግዜያት አንዳንዶች ተደርሶባቸው ሌሎች ግብራቸው እየገለጣቸው ከኛ ወገን አልነበሩምና ከኛ ዘንድ ወጡ ከኛ ወገን ቢሆኑስ ቅዱስ ዮሐንስ እንደተናገረው ከኛ ጋር ጸንተው በቆዩ ነበር ፤1ኛ ዮሐ.2፤19

ምዕመናንን ለማስኮብለል ከሚጠቀሙባቸው የተለያዩ የማስኮበለያ ሰልቶች አንዱ ከዚህ በፊት በስፋት ሲጠቀሙበት የኖሩትን ጥራዝ ነጠቅ የሆኑ ጥቅሶችን በመምዝ ለማደናገሪያነት በመጠቀም በእምነት የደከሙትን የመንጠቅ ሥራ ተወት በማድረግ ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እስከ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሚታዩ የአስተዳደር ክፍተቶችን እንደመነሻ በመጠቀም በቀጣይ ሌሎች ኑፋቄዎችን በማንሳት ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲጠሉ በማድረግ ለማሰኮብለል ጥረት ሲያረደርጉ ቆይተዋል አሁንም ከዚህ ሥራቸው አልተቆጠቡም፤ ይህንን እኩይ ተግባራቸውን ከኛ ወገን የሆኑና በሴራቸው ሳያውቁ የተጠለፉ ወጣቶችን በሰንበት ትምህርት ቤታችን ደረጃ ግለሰቦቹን ለይተን ከማወቅ በተጫማሪ የተለያዩ የአባቶችንና የወንድሞችን ምክር እንዲያገኙ ተደርገው ከተገባራቸው የታቀቡና የዕውቀት ክፍተቶቻቸውን እያሻሻሉ የመጡ ብዙ ወጣቶች ቢኖሩም አሁንም ድረስ በንቀትና ከኔ በላይ አዋቂ በሚል መታበይ ከነኑፋቄያቸው የሚመላለሱ እንዳሉ ሁሉ እንደ ወትሮው ወደ ውስጥ ዘልቀው በመግባት ወጣቶችን መንጠቅ ሲሳናቸው በየጎዳናው ፤በትምህርት ቤት ፤በመዝናኛ ስፍራዎች የሚገኙ ወጣቶችን በኑፋቄያቸው በማጥመድ ላይ ይገኛሉ በዚህ ሂደትም ቀላል የማይባሉ የከተማችን ወጣቶች በነዚህ የአምልኮ መልክ ባላቸው ኃይሉን ግን በካዱ አላውያን እየተወሰዱ ይገኛሉ ፤
ሆኖም ግን ለዚህ ሥራቸው አመቺ ከሆኑ ነገሮች መካከል፡-
1ኛ- ወጣቶች ቤተ ክርስቲያን ቀርቦ የእግዚአብሔርን ቃል ከመማር ይልቅ ለስጋቸው በማድላት በመዝናኛ ስፍራ ብቻ ማሳለፍና በሰንበት በሳምንት አንድ ቀን እንኳ ቤ/ክ መምጣት አለመቻላቸው ቤተ ክርስቲያን ልጆችዋን የት አግኝታ ማስተማር እንደምትችል ግራ የሚያጋባ መሆኑ፤
2ኛ-ብዙ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ቤተ-ክርስቲያን የማይልኩ ከመሆናቸው ባሻገር የት እንደሚውሉ እንኳን የማይከታተሉ መሆኑ፤
3ኛ- ለመማር የቀረቡ ወጣቶችም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ከሥር መሠረቱ አጠናቆና ታግሶ ከመማርና ራሳቸውንም ቅዱሳን መጻህፍትን በማንበብ ዕውቀታቸውን በማጎልበት ህይወት የሚያገኙበትን ቃለ-እግዚአብሔርን ከማወቅ በተጨማሪ ለሚጠይቋቸው መልስ ለመስጠት ከመዘጋጀት/1ኛጴጥ.3፤15/ መስነፍና የማውቀው ይበቃኛል ማለት ፤ የተሻለ ዕውቀት ያላቸውም ቢሆኑ መክሊታቸውን ከማትረፍ መዘግየታቸው ዋና ዋና ችግሮች ናቸው፡፡
በመሆኑም ወላጆች ልጆቻችሁን ለማሳደግ መክፈል ከሚገባችሁ ወጪ ከማይጠይቀው ኃላፊነትና ውለታችሁ አንዱ ልጆቻችሁን ወደ ቤተ እግዚአብሔር መላክ አንዱና ዋነኛው ነው ይህን ሳታደርጉ ቀርታችሁ ልጆቻችሁ በስነ-ምግባር ችግሮች ቢተበተቡ፤ በአሳሳቾች መናፍቃን ተነጥቀው ከመጸጸት ይልቅ ከወዲሁ ኃላፊነታችሁን ትወጡ ዘንድ አደራ እንላለን፡፡
ወጣቶች ሆይ ሀዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፤
‹‹ ወንድሞች ሆይ፥ መጠራታችሁን ተመልከቱ፤ እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች፥ ኃያላን የሆኑ ብዙዎች፥ ባላባቶች የሆኑ ብዙዎች አልተጠሩም››1ኛ ቆሮ.1፤26-28 ይላል በመሆኑም ለስጋ ከማድላት ይልቅ ለነፍስ ማድላት መልካም ነውና በተለይ አንዳንድ ወጣቶች ከአጓጉል ሱሳሱስ፤ ከዘፈንና ከጭፈራ በመራቅ ባዕላትን ጠብቆ ብቅ ከማለት ተቆጥባችሁ ለነፍሳችሁ ዋጋ በመስጠት ወደ ቤተ ክርስቲያን በመቅረብ ቃለ-እግዚአብሔርን ትመገቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ሥም እንለምናችኋለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
የአ/ነ/ደ/ል/ቅ/ጊ/ቤ/ክ ሰ/ት/ቤት

ምንም አስተያየቶች የሉም :

አስተያየት ይለጥፉ

comment