ቅዳሜ 12 ኤፕሪል 2014

ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ማቴ 21፤9
«ሆሳዕና» የአረማይክ ቋንቋ ሲሆን ትርጉሙም ‹‹እባክህ እርዳ፣ አሁን አድን» ማለት ነው።
ቅዱስ ዳዊት አስቀድሞ በመዝሙሩ ፣ማዳኑን በመሻት «አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አድን አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አቅና» ሲል ዘምሮለታል።መዝ.118 ፤25
እንዲሁም በዘፍጥረት 49፥10 ‹‹በትረ መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም፥ የገዥም ዘንግ ከእግሮቹ መካከል፥ ገዥ የሆነው እስኪመጣ ድረስ፤ የአሕዛብ መታዘዝም ለእርሱ ይሆናል። ውርንጫውን በወይን ግንድ ያስራል፥ የአህያይቱንም ግልገል በወይን አረግ፤ ልብሱን በወይን ያጥባል፥ መጎናጸፊያውንም በወይን ደም›› ተብሎ ተነግሮአል ፤
በትንቢትም «አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል» ዘካ. 9፤9
‹‹በፊቱ እንደ ቡቃያ ከደረቅም መሬት እንደ ሥር አድጎአል። መልክና ውበት የለውም፥ ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም» ኢሳ. 53፤2
ተብሎ ተነግሮአል
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሆኖ ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከ፥እንዲህም አላቸው፦ ‹‹በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ» ማቴ 21፤2 በማለት በውርጫይቱ ተቀምጦ ወደ ቤተ መቅደሱ በገባ ጊዜ ቤቱን የንግድ ቤት አድርገውት ነበር እርሱም ‹‹ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአል፥ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው›› ከዚያም በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አወጣ፥ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠ ፡፡

ዛሬም በመቅደሱ ውስጥ ተመሳስለው እየገቡ የራሳቸውን ጥቅም ከሚያጋብሱና በደሙ የተዋጀችን ቤተ ክርስቲያን በኑፋቄ ትምህርት ከሚያጎድፉ ሰዎች እግዚአብሔር እንዲጠብቅልን ልንጸልይና ልንተጋ ይገባል !

ምንም አስተያየቶች የሉም :

አስተያየት ይለጥፉ

comment