እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሳችሁ !
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከምታከብራቸው ዐበይት እና ንዑሳን በዓላት መካከል አንዱ በዓለ መስቀል ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በወርኃ መስከረም ብቻ በዓለ መስቀልን አራት ጊዜ ታከብራለች፡፡
የመጀመሪያው ምክንያተ ክብረ በዓል፣ በኢትዮጵያ ነግሦ የነበረው ዓፄ ዳዊት ከግብፅ ንጉሥና ሊቃነጳጳሳት የተላከለትን በቅዱስ ሉቃስ እጅ የተሳለችውን ስዕለ ማርያምን፣ በወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ የተሳለውን ኩርዓተ ርእሱን ፣ ሌሎች ንዋያተ ቅድሳትን እና የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ግማደ መስቀል የግብፅ እና ኢትዮጵያ ድንበር ከነበረችው አስዋን ከተባለችው ቦታ ተረክቧል፡፡
ንጉሡ የያዘውን በረከት ወደ ኢትዮጵያ ሳያደርስ ስናር በተባለው ቦታ ዐረፈ፡፡ ከጊዜ በኋላ የዐፄ ዳዊት ልጅ ዳግማዊ ቆስጠንጢኖስ የተባለው ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ተቀብሎ በደብረ ብርሃን፣ በየረር፣ በመናገሻ እና በልዩ ልዩ ተራራማ ቦታዎች ሲዘዋወር ቆይቶ “ መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ አኑር ” የሚል ራእይ ተገልጦለት ቅዱስ መስቀሉን በወሎ ክፍለ ሀገር በአምባሰል አውራጃ በግሸን ደብረ ከርቤ አስቀምጦታል ፡፡ መጋቢት ዐሥር ቀን ደብረ ብርሃን ሲገባ ብርሃን ስለወረደና ዐፄ ዳዊት ከግብፃውያን ጳጳሳት እና ንጉሥ እጅ መስቀሉን የተረከቡበትን ቀን በማዘከር የአድባራት እና የገዳማት ሊቃውንት ልብሰ ተክህኖአቸውን ለብሰው የብር መቋሚያ እና ጸናጽል ይዘው ወደ ነገሥታቱ ሔደው ተቀጸል ጽጌ እያሉ እያሸበሸቡ ጸሎተ ወንጌል ያደርሱ ስለነበር መስከረም ዐሥር ቀን የዓፄ መስቀል በዓል ተብሎ ይከበራል፡፡
ሁለተኛው መስቀሉን በቁፋሮ ያገኘችው ንግሥት እሌኒ ደመራ ያስደመረችበት እና የእጣኑ ጢስ መስቀሉ ወደተቀበረበት ድልብ አከል ተራራ ያመለከተበት ዕለት መስከረም ዐሥራ ስድስት ቀን በመሆኑ የመስቀል ደመራ በዓል በዚሁ ዕለት ይከበራል፡፡
መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን ደግሞ ቁፋሮ ያስጀመረችበት ዕለት ሲሆን መጋቢት ዐሥር ቀን መስቀሉን አግኝታለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን አሠርታ፣ መስቀሉን አስገብታ ቅዳሴ ቤቱን ያከበረችበት ዕለት ግን መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን ነው፡፡ የመስቀሉ መገኘት ጥንተ በዓሉ መጋቢት ዐሥር ቀን ቢሆንም አባቶቻችን በታወቀና በተረዳ ነገር ዋናው የመስቀል በዓል የሚከበርበት ዕለት መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን እንዲሆን አድርገዋል፡፡ በመጨረሻም መስከረም ሃያ አንድ ቀን በዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት በግሸን ደብረ ከርቤ መስቀሉ ያረፈበት ዕለት ስለሆነ
“በልደቱ ፍስሐ ፤በጥምቀቱ ንስሐ፤በመስቀሉ አብርሃ፤ ”እያልን በማኅሌት፣ በዝማሬና በቅዳሴ ለዘለዓለም ስናከብረው እንኖራለን ፡፡የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው 1ኛ ቆሮ 1፤18 ተብሎ እንደተጻፈ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ያለመስቀል የሚከናወን ሥርዓት የለም፡፡ ከካህናት አክሊል ከመነኮሳት አስኬማ ከእናቶች ቀሚስ እስከ አባቶች እጀጠባብ ድረስ የመስቀል ምልክት እያደረግን በሰውነታችን እየተነቀስን በአንገታችን እያሰርን ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር እንገልጣለን፡፡
እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን እውነተኛ ፍቅር በተለያየ መንገድ አሳይቷል፡፡ ሰማይና ምድር የእርሱ የሆነ አምላክ በከብቶች ግርግም ተወለደ፡፡ የተነገረው ትንቢት የተቆጠረው ሱባዔ ሲያልቅ በመስቀሉ ተፈጸመ ብሎ ሕይወትን በመስጠት ሞታችንን በመውሰድ ፍቅሩን ገለጠ መስቀል ፍቅረ እግዚአብሔርን የሚያሳስበን የስብከታችን ርእስ የኑሮአችን መርሕ ስለሆነ በዓመት አንድ ጊዜ ወይም ሁለት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ዘወትር እናስበዋለን፡፡
ከዐሥራ አራተኛው መቶ ክፍለዘመን ጀምሮ በደጋግ ነገሥታቶቻችን አማካይነት ቅዱሱ መስቀል ወደ ሀገራችን እንዲገባ የዘወትር ጥረት አድርገዋል፡፡ የለመኑትን የማይረሳ የፈለጉትን የማይነሣ አምላክ መስቀሉ በሀገራችን እንዲቀመጥ ፈቃዱ ሆኖአል፡፡
"ውእቱ ዝንቱ መስቀል ወቦቱ ንትመካህ ከመ ንሰብሖ … እንሰግድለት ዘንድ የምናከብረው፣ እናከብረው ዘንድ የምንመካበት ይህ መስቀል ነው፡፡" /ጸሎተ ኪዳን/ እንደተባለው ሕይወትና ድኅነትን ያገኘንበት የሲኦልን እሳት ተሻግረን ወደ ገነት የገባንበት የአምልካችን ፍቅር የተገለጠበት ዐውድ በመሆኑ መስቀሉን እያሰብን በዓሉን እናከብራለን፡፡
በሐፁረ መስቀሉ የጠበቀን በደመ መስቀሉ የዋጀን አምላክ ይክበር ይመስገን፡፡
ምንጭ ፡-የማህበረ ቅዱሳን ገጸ-ድር 2004 ዓ/ም ዕትም በከፊል የቀረበ
ምንም አስተያየቶች የሉም :
አስተያየት ይለጥፉ