ረቡዕ 21 ኦገስት 2013



እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የዕርገት በዓል በሰላም አደረሳችሁ !  
ይህ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሞት የመነሳት ምስጢር ለበዙዎች አልዋጥላችሁ ብሏቸዋል፡፡ እንደውም ይህን ስንናገር አምላክ ያደረግናት ይመስላቸዋል፡፡ሌሎች ደግሞ እሷን ከጌታችን ጋር እኩል ለማድረግ እየጣርን ያለንና የፈጠራ ወሬ እያወራን ለማሳመን የምንሞክር ይመስላቸዋል ይህ ሁሉ ግን በዕርግጥ ትክክለኛ አስተሳሰብ እይደልም፡፡መጽሀፍ ቅዱስ ላይ ሞትን እንኳ ያልቀመሱ እስከ አሁን እንዳሉ ይነገራል፡፡ ለምሳሌ ያህል ሄኖክ አልሞተም፡፡ “ሄኖክም አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ አልተገኘም እግዚአብሔር ወስዶታልና”፡፡ ዘፍ.5፤27 ከእግዚአብሔር ጋር አካሔዱን በማድረጉ ከተወሰደው ሔኖክ ይልቅ በእግዚአብሔር ጸጋ የተሰጣት መንፈስ ቅዱስ የጸለለባት  አምላካችንን  የወለደች እመቤታችን ተነስታለች አርጋለች ቢባል ምን ይገርማል ኢያሱ ከአሞራውያን ጋር  በተዋጋ ጊዜ ጸሀይ እንዳትጠልቅ በማድረግ አቁሟታል፤ እያሱ.10፤12 ይህ በማን ሆነ እንዴት ሆነ ብለን ልንቃወመው አንችልም ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር ማድረግ እንደሚችል ብቻ እናውቃለን፤ መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ሀዋርያትን ሲያስተምር እውነት እላችኋለሁ የሰው ልጅ በመንግስቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ ከዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱት እንዳንዶች አሉ ማቴ 16፤26 ኤልያስ በደመና ተነጥቋል፤2ኛ ነገ. 2፤11 ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል “የሚያምንብኝ ቢኖር እኔ የማደርገውን ብቻ ሳይሆን ከእኔም የበለጠ ያደርጋል” ዮሐ 14፤12 ብሏል ይልቅ የአምላክ እናት ከሁሉ የተለየሽ የተባለችና ከነብያትና ከሐዋርያት ትበልጫለሽ የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ልጇ ዘንድ ማረጓ ለአንዳንዶች ለምን አይዋጥላቸውም እንዴትስ በዚህ ነገር ይሰናከላሉ?
የእመቤታችን የቀብር ሥነ ሥርዓት በተፈጸመ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ቶማስ አልነበረምና ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን በተቀበረች በሦስተኛው ቀን እንደ ልጅዋ ትንሣኤ ተነሥታ ስታርግ ያገኛታል፡፡ እመቤታችንም ከእርሱ በቀር ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሳኤዋን እንዳላዩ ነግራው ምልክት ይሆነው ዘንድ ሰበኗን /መግነዟን/ ሰጥታዋለች ሐዋርያው ቶማስም ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ እመቤታችንን ቀበርናት ብለው ነገሩት  እርሱም “ሞት  በጥር  በነሐሴ    መቃብር  እንዴት ይሆናል?” ቢላቸው፡፡ “የጌታን ትንሣኤ ተጠራጠርክ አሁንም ለምን  ታምንምን;”  ብለው በቅዱስ ጴጥሮስ መሪነት ወደ እመቤታችን  መካነ መቃብር  ይዘውት  ሄደው  መቃብሩን  ቢከፍቱ ሥጋዋን አጡት፡፡ ደነገጡም፡፡  ቶማስም  “አታምኑኝም ብዬ እንጂ እመቤታችን ተነሥታ ዐርጋለች” ብሎየሆነውን ሁሉ ነገራቸው፡፡ ለማረጋገጫ ምልክት እንዲሆን የሰጠችውን ሰበኗን አሳያቸው፡፡ሰበኗን /መግነዟን/ ለበረከት ቆራርጠው  ከተከፋፈሉ በኋላ ወደ የአህጉረ ስብከታቸው ሄደዋል፡፡ሐዋርያትምእርሱ (ቶማስ) ትንሣኤሽንና ዕርገትሽን አይቶ እኛ ለዚህ ዕድል ሳንበቃ እንዴት እንቀራለን?” በማለት አዝነው ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምረው ሱባኤ ገቡ፡፡ በመጨረሻም ነሐሴ 16 ቀን ጌታችን ጸሎታቸውን ተቀብሎ እናቱን ቅድስት ድንግል ማርያምን መንበር፣ ራሱን ሠራዒ ቄስ፣ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ረዳት ካህን፣ ቀዳሚ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስን ሠራዒ (ዋና) ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ ሁሉንም ከአቆረባቸው በኋላ ዕርገቷን ለማየት አብቅቶአቸዋል፡፡  
እግዚአብሔር ከእመቤታችን ትንሳዔ በረከት ያሳትፈን ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
  

ምንም አስተያየቶች የሉም :

አስተያየት ይለጥፉ

comment